የዘርፍ ማህበራችን ፕሬዚዳንት አቶ ብያኔ ቱፋ የጠቅላላ ጉባኤውን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያስጀመሩ ሲሆን በንግግራቸውም “የዘርፍ ማህበራችን አባል ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ተቋቁመው የምርት ሂደታቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ጥረት የሚያስመሰግናቸው እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲሁም የመንግስት ፖሊሲ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ጉልህ ሚና ያላቸው መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻዎች ሊደረግላቸው ይገባል ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የዕለቱ የክበር እንግዳ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ ዶ/ር ሚልኬሳ ጃገማ ባሰሙት ንግግር የኬሚካል ኢንዱስትሪ የሁሉም ኢንዱስትሪ እናት ነው ይባላል ስለሆነም እንደመንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡ እስካሁን ለጨርቃጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪ ነበር ትኩረቱ ከዚህ በኋላ ግን የኬሚካል ኢንዱስትሪው ማደግና መስፋፋት ለሌላው ኢንዱስትሪ መጋቢ ስለሆነ ትኩረት ሰጥተን ለማገዝ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው የ2018 ዓ.ም ዕቅድ እና የ2017 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርበው ውይይት ከተደረገበት በኋላ የጸደቀ ሲሆን አባል ኢንዱስትሪዎች እያጋጠሟቸው ያሉ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች በጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ተነስተው ሀሳብና አስተያየት ከተንሸራሸሩ በኋላ አቅጣጫ ተቀምጦባቸዋል፡፡ በመጨረሻም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ተካሄዶ የእለቱ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠናቋል፡፡



